መግቢያ ፦
ከቅርብ ዓመታቶች ወዲህ «ቅባት» የሚለው ቃል በክርስትናው ዓለም ( ማለትም በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አማኞች ዙሪያ ማለቴ ነው) በብዛት የሚነገር፣ ተካታታይ ትምህርት የሚሰጥበትና የሚዘመርበት ርዕሰ ጉዳይ የሆነ መጥቷል። ቃሉ ለሁላችንም አዲስ ባይሆንም፣ በዘመናችን ጥቅም ላይ እየዋለ ላለበት ሓሳብ ግን አንዳንዶች እንግዶች መሆናችን አልቀረም። ይህንን ጥያቄ አድርገን ስንጓዝ ከበስተጀርባው አንድ የተቀናጄና የተደራጀ አስተምህሮ አንዳለ መገንዘብ እንችላለን። አካሄዱም በመስቀል ሞቱ እኛን የዋጀንን ጌታ ከዐይናችን ፊት እየሰውረ፣ ሰውን ወደ ማንገስ የሚያቀርብ አካሄድ ነው። በዚህ ሳቢያ በቤተ ክርስቲያን “አምልኮተ ሰብ” እንዳይስፋፋ ያሰጋል። እንዲህ መባሉ አሳሳቢነቱን ለማጉላት ነው እንጂ ሌላ ለምንም ዓላማ አይደለም። ስለዚህ በቅዱሳን መካከል አንድ ግራ የሚያጋባ ነገር ሲከሰት፣ ቅድሚያ መጽሓፍ ቅዱስ ስለ እዚህ ጉዳይ ምን ያስተምራል? ዘመናችንስ የሚለው ነገር ምንድነው ? የሚሉትን አውራ ጥያቄዎች በማንሳትና በመጠየቅ ወደ መጽሓፍ ቅዱስ ትምህርትና ሥልጣን መመለስ ለወንጌል አማኞች ታሪካዊ ባህላችን ነው። እንግዲህ የዛሬውን ትምህርታችንን የምንመለከተው በዚህ ዓላማና ሓሳብ ይሆናል።
ስለ ቅባት የመጽሓፍ ቅዱስ ትምህርት፦
«ቅባት» የሚለው ቃል ያለውን መጽሓፍ ቅዱሳዊ አገባብ ልብ በማለት የተመለከትን እንደሆነ፣ ቃሉ በቅዱሳት መጽሓፍት ውስጥ ለተለያዩ ዓላማዎች ጥቅም ላይ ውሎ እናገኜዋለን። ይኽውም አንድን ዕቃ ወይንም አንድን ሰው ለእግዚአብሔር የተቀደሰ አገልግሎት የተለየ መሆኑን ለማሳየት ቃሉ በዘጸ 29፣ 29 ፤30፣ 26፤ዘሌ 4፣ 3 ጥቅም ላይ ውሏል። ለሰውነት እንክብካቤ ሰዎች የሚታሹበትን ፈሳሽ ቅባት ለማመልከት ደግሞ ቃሉ በማር 14፣ 8 ላይ ቃሉ አገልግሎት ላይ ውሏል። እንዲሁም ሕሙማን እንዲፈውሱ ለማድረግ ከእምነት ጸሎት ጋር ተያይዞ የሚቀባን ፈሳሽ ዘይት ለማሳየት ደግሞ በያዕ 5፣ 14 ላይ ቃሉ ጥቅም ላይ ውሎ እናገኘዋለን። በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በተለዋጭ ዘይቤአዊ አነጋገር እሳት፣ ውሃ፣ ርግብ......ወዘተ የሚሉት መጠሪያ ተጠርቷል። እነዚህ የተለዋጭ ዘይቤያዊ ንግግሮች መንፈስ ቅዱስን በመግለጫነት እንደሚያሳይ ሁሉ፣ በተመሳሳይ መልኩ «ቅባት» የሚለውም ቃል መንፈስ ቅዱስን ለማሳየት የአዲስ ኪዳን ጻሓፊዎች ቃሉን ተጠቅመውበታል። ዬሐንስ በመልክቱ « እናንተ ግን ከእርሱ ከቅዱስ ቅባት አላችሁና ሁላችሁም እውነትን ታውቃላችሁ » ይላል( 1ዬሐ 2፣ 20) ። አማኞች በክርስቶስ ሲያምኑ ከቅዱስ ቅባት ይቀበላሉ። ይኽውም መንፈስ ቅዱስን ማለት ነው። እርሱ ወደ እውነት የሚመራ አምልክ በመሆኑም፣ በእርሱ አማካይነት እውነትን ያውቃሉ ፤ ይማራሉም።
ቅባት በሁለቱ ኪዳናት ያለው አጠቃቀም፦
ብሉይ ኪዳን፦
በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ ‘’ቅባት’’ የሚለው ቃል የተለመደ አጠቃቀሙ አንድን ሰው ወይም አንድን ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ( የተለየ) መሆኑን በማመልከት ረገድ ነበር። ስለ «መቀባትና» «ስለ ቅባት» በብሉይ ኪዳን ያለውን ትምህርት ስንመረምር፣ ቃሉ ካህናትን ፣ ነገሥታትን፣ ነቢያትንና ቁሳቁሶችን ለእግዚአብሔር ሥራ መለየታቸውን ወይም መቀደሳቸውን ለማሳየት ጥቅም ላይ እንደዋለ እናስተውላለን። እንግዲህ ይህንን ሓሳብ እንደ ቅድመ- ግንዛቤ በመያዝ ነው «ቅባት» የሚለው ቃል በብሉያት መጽሓፍት ያለውን አጠቃቀም የምንመለከተው፦ በብሉያት መጽሓፍ «ቅባት» የሚለው ቃል በዐራት መንገድ ጥቅም ላይ ውሏል። ይኸውም ፦
በዚያ ኪዳን ያገለግሉ የነበሩ ካህናት፣ ለእግዚአብሔር መለየታቸውን ለማሳየት፦
በቀደመው ኪዳን ውስጥ ካህናት ለእግዚአብሔር አገልግሎት ሲለዩ፣ በተጨማሪም ካህናቱ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን የኃጢአት ሥርየትን ሲያቀርቡ፣ ኪዳኑ ይፈቅደው ለነበረው ኅይማኖታዊ ሥርዐት መለየታቸውን ለመግለጽ ወይም ለማሳየት ይቀቡ ነበር ( ዘጸ 28፣ 41፤ 29፣ 1፤ 30፣30፤ 40፣ 13- 15፤ ዘሌ 6፣ 1 ፤ 7፣ 35- 36፤ 8፣ 12፤ ዘኁ 3፣3፤ ዘሌ4፣ 3-5፤ 6፣ 22፣ 16,32፤ 21፣ 10)።
1.1.2 የቁሳቁሶችን ለእግዚአብሔር አገልግሎት መለየትን ለማሳየት ቃሉ በጥቅም ላይ ውሏል፦
በብሉይ ኪዳን የተለያዩ ቁሳቁሶች ማለትም ድንጋይ( ዘፍ 28፣ 18፤ 31፣ 13) ፤ መሠዊያ ( ዘጸ 29፣ 21፤ ዘሌ 8፣ 10፤ ዘኁ 7፣ 1-10) የመገናኛ ድንኳን፣ የቃል ኪዳኑ ታቦትና በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያሉት ቁሳቁሶች በሙሉ፣ ለኃይማኖታዊ ሥራ መለየታቸውን ለማመልከት ይቀቡ እንደ ነበር እንመለከታለን ( ዘጸ 30፣ 22፤ 40,9፤ ዘሌ 8፣ 10፣ ዘኁ 7፣ 1) ። እነዚህ ሁሉ ቁሳቁሶች የሚቀቡት ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለዩ ወይም የተቀደሱ መሆናቸውን ለማመልከት ነበር።
ከዚሁ ጋር አያይዘን የምንመለከተው ሌላው ነገር እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎችም በተለያየ ዓላማ ራሳቸውን፣ ሌሎች ሰዎችንና ዕቃዎችን ይቀቡ ነበር።ለምሳሌ ዳንኤል ሦስት ሳምንት በጸለየበት ጊዜ« አልተቀባሁም ነበር» ሲል፣ በዘመኑ ሕብረተሰቡ ራስን ለማውዛትና ቆዳን ለመንከባከብ የሚቀቡትን የቅባት ዓይነት ለማሳየት የተጠቀሰ መሆኑ እሙን ነው ።
በአገራችን ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዓመታት አባቶች ፊሎቪር ወይም በልጅግ ጠመንጃቸውን በዘይት እንደሚወለወሉ፤ በ2ሳሙ 1፣ 21 ላይ የሳዖል ጋሻ ጥንካሪውን ይዞ እንዲቀመጥ ዘይት ይቀባ እንደ ነበረ ተገልጿል ። በጥንት ዘመን ይኖሩ በነበሩ የአይሁድ ማህበረሰብ ዘንድም አንድ የተከበረ እንግዳ በግብዣ ላይ ሲገኝ፣ ለእንግዳው ያላቸውን አክብሮት ለመግለጸ ሲባል፣ ከገበታው ዝግጅት በተጨማሪ ዘይትን ቀብቶ ማስተናገድ የአይሁዶች የተለመደ ወግና ሥርዐታቸው ነበር ( መዝ 23፣ 5፤ ሉቃ 7፣46 ፤ ) ።
1.1.3 ነገሥታት ለእግዚአብሔር አገልግሎት መለየታቸውን ለማሳየት ቃሉ በጥቅም ላይ ውሏል፦
በብሉይ ኪዳን በእስራኤል ሕዝብ መካከል የምንመላከታቸው ነገሥታት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማስተዳደርና ለመምራት እንዲሁም በሕዝቡ ላይ ለመፍረድ በእግዚአብሔር የተለዩ መሆናቸውን ለማሳየት ይቀቡ ነበር( መሳ 9፣ 7 -15፤1 ሳሙ 9፣ 16፤ 10፣ 1-15፤ 15፣ 17፤ 16፣ 3፤ 12-16፤ 4፣ 24፤ 6፣ 26፣ 9- 11፤ 2ሳሙ 1፣ 14-16 ፣ 3፣ 39፤ 12፣ 7፤19፣ 21፤1ነገ 1፣ 34- 45፤ 19፣ 5-16 መዝ 20፣ 6 )።
ለዚህ ዓይነት አገልግሎት ወይም ንግሥና ሰዎችን «ለዩልኛና ቀቡልኝ »ብሎ የሚያዘው ራሱ እግዚአብሔር ነበር( 1 ሳሙ 16፣ 6፤ 24 ፣ 6፤ 26፣ 9-11፤ 1ሳሙ 1፣ 14-16፤3፣ 39፤12፣ 7፤19፣ 21 ) አንድ ሰው ይህንን ዓይነቱን «ቅባት» መቀባት ስለፈለገ ወይም ሰዎች ተሰብስበው እንቀባህ ስላሉት የሚገባው የቅባት ዓይነት አልነበረም።
1.1.4 ነቢያት ለእግዚአብሔር አገልግሎት መለየታቸውን ለማሳየት ቃሉ በጥቅም ላይ ውሏል፦
ከብሉይ ኪዳን መጸሓፍ አንዳንድ ሰዎች ለነቢይነት አገልግሎት ሲለዩ ይቀቡ እንደ ነበር እናነባለን( 1ነገ 19፣ 16፤ ኢሳ 6፣ 1) በዚህ ዓይነት ኤልያስ ኤልሣዕን ሲቀባው እንመለከታለን። ይሁን እንጂ ኤልያስ ኤልሣዕን የቀባው በራሱ ተነሳስቶ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር እንዲቀባው ስላዘዘው ነው ። ( 1ነገ 19፣ 16)። በዚያ ኪዳን እግዚአብሔር ቀቡልኝ ሲል ብቻ ሰዎች ይቀቡ ነበር እንጂ ማንም መቀባት ስላማራው አይቀባም ነበር። ደግሞም እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በሥርዐታዊው ሕግጋት ውስጥ ተካትቶ የሚከናወን ተግባር ነበር።
እንግዲህ ከዚህ በላይ ለማንሳት እንደተሞኩት ቅባት በብሉይ ኪዳን አገልገሎት ላይ ውሎ የምናገኜው በዚህ ዓይነት መልኩ ብቻ ነው። ደግሞም ለዚህ ተግባር እግዚአብሔር ብቻ የሚጠቀምበት የተቀደሰ« ቅባትና ዘይት» እንደ ነበረ ከዘጸ 30፣ 22- 33 ከተቀመጠው የመጸሓፍ ቅዱስ ሓሳብ መረዳት እንችላለን። ደግሞም ይህን ዓይነቱን ዘይት ማዘጋጄትና መጠቀምም ለማንም አልተፈቀደም ነበር። ደግሞም ሲጠቀምበት በተገኘው ላይ ጽኑ ቅጣትና ከኪዳን ሕዝብነት እንደሚለይ በጽኑ ተደንግጓል።
«ካህናትና ነገሥታት በዚህ ዘይት መቀባታቸው( ዘጸ 30፣ 30፤ 1ነገ 1፣ 39፤ 1ሳሙ 10፣ 1፤ 16፣ 1) እግዚአብሔር ለተለያዩ ቢሮዎች የተለያዩ ቅባቶችን ይጠቀም እንዳለነበረ አመልካች ነው። በትንቢተ ዘካርያስ 4፣ 14 ላይ «እርሱም። በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙት ሁለቱ የተቀቡት እነዚህ ናቸው አለኝ»። የሚል ቃል እናገኛለን።
የዚህን ምእራፍ ዐወደ ምንባባዊ ሓሳብ ተከትለን እንሂድ ካልን፣ በዚህ ክፍል «ሁለቱ የተቀቡት» የተባሉት የሚያመለክተው በምዕራፍ ሦስት ላይ የተጠቀሰውን «ካህኑን ኢያሱን» እና በምዕራፍ አራት ደግሞ ከዳዊት የንግሥና ቤተሰብ የሆነውን «ዘሩባቤልን» ለማመልከት ነው። በዚህ ክፍል የሚታዩት የክህነትና የንግሥናው ቢሮዎች ሲሆኑ፣ ሁለቱም በዘካርያስ ራዕይ ውስጥ በወይራ ቅርንጫፎች ተመስለዋል። ሁለቱም የወርቅን ዘይት ያፈሳሉ፤ አንዳንድ አስተማሪዎች ዘይቱን መንፈስ ቅዱስ ነው ይሉናል። ይሁን እንጂ በዚህ ክፍል ዘይቱ የወርቅ መባሉ የተለየ ኃይል የሚለቀቅበት «ቅባት» መሆኑን ለማመለክት አይደለም። በቢሮዎቹ ላይ ያስከተለው ምንም ዓይነት ለውጥ አልነበረምና ነው። ምክንያቱም ኢያሱም ከአሮን የክህነት ሥርዐት አልወጣም። እንደ መልከ ጼዲቅ የክህነት ሥርዐት«አንተ ለዘላለም ካህን ነህ» ተብሎ የተነገረለት ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።
ለነቢይነት አገልግሎት ኢልሳዕ ሲለይ የተቀባ ቢሆንም፣ ይህ ለነቢያት ሁሉ የተለመደ አልነበረም። በዚያ ኪዳን ውስጥ አንድን ሰው ለአገልግሎት የሚመርጥና በመቀበት የሚለይ አሁንም ቢሆን እግዚአብሔር ራሱ ነበረ እንጂ ሰው አልነበረም ( 1ነገ 19፣ 16) ።
ከዚሁ «ቅባት» ከሚለው ቃል ጋር በተያያዘ መንገድ አንድ ሓሳብ እንሰማለን። ይኸውም« «የቀባኋቸውን አትንኩ»» የሚለው ትእዛዛዊ ቃል ነው (መዝ 105፣ 15) ። የዚህ ቃል ትርጉም በክፍሉ የተቀመጠው ምን ዓይነት ሓሳብ በመያዝ ነው? እስኪ በመቀጠል የክፍሉን ሓሳብ እንመለከት፦
1.1.5 የተቀባውን ስለ አለመንካት የተዘመረው ዝማሬ ዐውደ ምንባባዊ ትርጉም፦
ቃሉ የሚገኘው መዝ 105፣ 15 ላይ ነው ። መዝሙር 105 እግዚአብሔር የከነዓንን ምድር ለአብርሃምና ዘሮች በመስጠት፣ የገባውን ቃል ኪዳን የፈጽምና የማዳን ሥራውንም ሁሉ በተግባር የገለጸ ታማኝ አምላክ በመሆኑ፣ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩትና በእርሱ እንዲታመኑ ለማድረግ፣ የቀረበ ማበረታቻ ዝማሬ ነው። ዝማሬው የተዘጋጅው በአንድ ሌዋዊ ሲሆን፣ እስራኤላውያን ከሚያከብሯቸው በዓላት በአንዱ ይኽውም በዳስ በዓል ላይ የሚዘመር መዝሙር እንደ ነበር ይነገራል።
እንግዲህ «የቀባኋቸውን አትንኩ» የሚለውን ሓረግ የምናገኘው በዚህ ክፍል በቁጥር 15 ላይ ነው ። በእኛ ዘመን ይህ ሐረግ ከዐውደ ምንባቡ ተነጥሎ በጥቅም ላይ ውሎ የምናገኘው፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ሆኑ የቃሉ አገልጋዬች አንድ ጥፋት አጥፍተው ሲገኙ፣ ከተጠያቂነትና ከወቀሳ ለማምለጥ በማሰብ የመከላከያና የማስፈራሪያ ሠይፍ አድርገውት ነው።
በመሠረቱ የእግዚአብሔር ቃል መሪዎችንም ሆነ ፣የቃሉን አገልጋዮችን በአገልጋይነታቸው ብቻ ስህተት ከመስራት ነፃ ሊሆኑ እንደሚችሉ አያስተምርም። አሮን የእስራኤልን ሕዝብ ለጣዖት አምላኪነቱ ረሃብ የወርቅ ጥጃ ሠርቶ በማቅረብ ስቶ አስቷል( ዘጸ 32፣ 1- 35)፡፡ ጴጥሮስ « አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ» የሚለውን መገለጥ ካመጣ በኋላ፣ መሲሑ መከራን እንደሚቀበል ሲያስተምራቸው፣ ሳይውል ሳያድር ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ የሆነ ሓሳብ በማሰብና በዚህ የክፉውን ምክር በማስተናገድ ኢየሱስን « እንዲህ ዓይነት ነገር ፈጸሞ አይድረስብህ እያለ ለመገሰጽ» ጊዜ አልወሰደበትም። ኢየሱስም የፊተኛው መገለጥ ከአብ ነው እንዳለው የኋለኛውንም የመረዳት ምንጭ ከአብ ነው አላለውም( ማቴ 16፣ 16-21)። አገልጋዬች ሊሳሳቱ ይችላሉ። አገልጋይነት በራሱ ፍጹምነትን አይሰጥም።
ወደ ተነሳንበት ጥቅሱ መሠረታዊ ሓሳብ ስንመጣ« ማንም ግፍ እንዳይፈጽምባቸው አልፈቅድም፤ ስለ እነርሱ ነገሥታትን እንዲህ ሲል ገሰጸ የቀባኋቸውን አትንኩ፣ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ» የሚለው ጥቅስ ከተጠያቂነት ለመዳን መጠቀሱ ነው። ትዕዛዛዊ ሓሳቡ የሚገኝበትን ዐወደ - ምንባብ ሰፋ አድርገን እንመልከት ካልን ፣መዝ 105፣ 1-15 ያለው ክፍል በ 1ኛ ዜና 16፣ 8-22 ካለው ሓሳብ ጋር ይያያዛል። መዝሙሩ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ቀን የተዘመረ ነው። ክፍሉ በግልጽ እንደሚናገረው የእስራኤል ታሪክ ባጭሩ የተወሳበት ክፍል ነው። የኪዳኑ ሕዝብ እግዚአብሔር አምላክ ሕጉንና ተስፋውን የሰጠው ሕዝብ ነው። በዚህ ሕዝብ መካከል ርዕሳነ- አበው ( ፓትሪያልክ ) በመባል የሚታወቁት አብርሃም፣ ይስሃቅና ያዕቆብ የዚህ ሕዝብ መገኛ አባቶች ናቸው። ይህ ጥቅስ የሚናገረው የእስራኤል ሕዝብ መገኛ አባቶች ስለ ሆኑት እንጂ ስለ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች አይደለም። እግዚአብሔር በዚህ ኪዳን ውስጥ አትንኩት ያለው ይህንን ምርጥ የሆነ ሕዝቡን ነበር። ከዚህ ውጭ ቃሉን ከተጠያቂነት ለመዳን ስልን ለራሳችን የምንጠቅሰው ክፍል አይደለም።በእርግጥ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዬች ማለትም የቃሉ ሰባኪና አስተማሪዎች ማለቴ ነው፤ ሊከበሩ ይገባል። ለእነርሱ እሽ ብሎ መታዘዝና መገዛትም ክርስቲያናዊ ኃላፊነት ነው። በእነርሱም ላይ ያለ ምስክር የትኛውንም ዓይነት ክስ መቀበልም አይገባም( 1ጢሞ5፣ 17-20) ነገር ግን ሲያጠፉ መጠየቅ መመከርና መገሰጽ አለባቸው። ጳውሎስ ኬፋን ከእውነት መንገድ በወጣ ጊዜ ፊት ለፊት ገሰጸው( ገላ 2፣ 11) ። ከዚህ ውጭ ይህንን ጥቅስ እየመዘዙ ከተጠያቂነት ማምለጥ ተገቢ አይመስለኝም ።
1.1.6 ቅባትና መንፈስ ቅዱስ፦
እግዚአብሔር ዳዊትን በመቀባት ለንግሥና በለየው ጊዜ መንፈሱን ሰጥቶት ነበር( 1ሳሙ 16፣ 13)። በኢሳ 61፣ 1-4 ላይም የተገለጸው አገልጋይ እግዚአብሔር ለአገልግሎት ሲለየው መንፈሱን በላዩ በማድረግና በመለየት እንደቀባው ነቢዩ ኢሳይያስ ይናገራል። በኋላም ይህ ትንቢት፣ በትንቢታዊ ሁለትዬሽ ገጽታው በቀጥታ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ጋር በመያያዝ በወንጌላት ተቀምጧል( ሉቃ 4፣ 18-19)። ቅባት የሚለው ቃል መንፈስ ቅዱስን ነው።
1.1.7 ቅባትና መሲሁ፦
እግዚአብሔር በቀባቸው በካህናትና በነገሥታት ምሳሌነት (ጥላነት) በመጠቀም በፍፃሜው ዘመን አንድ የተቀባ ሰው እንደሚመጣ አስቀድሞ አመልክቷል። እርሱም «መሲሕ» በመባል ይታወቅ ነበር። ሉቃስ በወንጌሉ ስለ ስም ዖን ሲናገር «የተቀባውን ሳያይ እንዳይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ»( ሉቃ 2፣ 26) ተብሎ በተነገረው ሓሳብ ውስጥ « የተቀባውን» የሚለው ቃል ለአንዴና ለመጨረሻ ስለ ተቀባው መሲሕ እንደሚናገር ያመለክታል።ብዙዎች እየተቀቡ የሚመጡ ቢሆን ኖሮ «የተቀባውን» የሚለው ቃል ማንን ለማለት እንደሆነ ግልጽ ባልሆነልን ነበር።
1.2 በአዲስ ኪዳን፦
ብሉይ ኪዳን ብቻ አይደለም፤ አዲስ ኪዳንም ስለ ቅባት ይናገራል። አስተምህሮውን በተመለከተ ወደ አንድ ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚቻለው ርዕሰ ጉዳዬችን በየተገለጹበት ኪዳናትና በየዐውደ ምንባባቸው ያላቸውን ትርጓሜ ይዘን ስለ ሆነ፣ አዲስ ኪዳንም ስለ ቅባት የሚያስተምረውን ትምህርት መመርመር ያስፈልጋል።
1.2.1 ፈሳሽ ቅባትን አስመልክቶ ቃሉ ጥቅም ላይ ውሏል፦
ተዳሳሹን ፈሳሽ ቅባት አስመልክቶ እንደ ብሉይ ኪዳኑ በአዲስ ኪዳንም በሁለት መንገድ ቃሉ ጥቅም ላይ ውሎ እናገኜዋለን። ይኽውም እንግዳን ለመቀበልን( አክብሮትንና ፍቅርን ለመግለጸ) እንዲሁም ሰውነትን ለመቃብር ለማዘጋጅት ነው (ማቴ 26፣ 7፣ ሉቃ 7፣ 38፤ማር 14፣ 8)።
በክርስትና እምነት ልምምድ ከፈውስ ጋር ተያይዞ በማር 6፣ 13፤ ያዕ 5፣ 14 ላይ ተቀምጧል። በማር 6፣ 13 ላይ ደቀ መዛሙርቱ ብዙ ድውዬችን ዘይት እየቀቡ እንዲፈውሱ የተመለከተ ቢሆንም፣ በሐዋርያት ሥራ ላይ ተገልጸው የምናገኛቸው ብዙ የፈውስ ታሪኮች ግን ሐዋርያቱ ቋሚ ልምምዳቸው እንዳላደረጉት ያስረዳሉ።
በያዕ 5፣ 14-15 ላይ የአማኙ ፈውስ ከሚደረግለት የእምነት ጸሎት ጋር የተሳሰረ መሆኑ ሊሰመርበት የተገባ ነው። ይህ ዓይነቱ በሽታን በዘይት የመቀባት ልምምድ ለብዙ ምዕተ ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የቀጠለ ቢሆንም ከዘጠነኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ አንድ ሰው እንደሚያድን ሲረጋገጥ ለነፍሱ ጥቅም እየተባለ ይቀባ ጀመር። ከዚ ጊዜ አንስቶ በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለሞተ ሰው የሚፈጸምለት ሥርዐት ሆነ። በቤተ ክርስቲያን የተሓድሶ ወቅት ግን ይህ ዓይነቱ ሥርዐት በሓዳሲያኑ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። አሁን በዘመናችን በሽተኛ ያልሆነውን ሰው ሁሉ ዘይት እየቀቡ የመጸለይ ሆነ፣ የተጸለየበትን ዘይት በየአማኙ ቤት የማስቀመጥ ልምምድ በአዲስ ኪዳን ውስጥ መነሻ አናገኝለትም። ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ያለው ትልቁ ፈተና በአንድ ወቅት እግዚአብሔር የሠራበትን አንድ ነገር የሕይወት ዘመን ቋሚ መመሪያና አስተምህሮ ማድረግ ነው።
1.2.2 መንፈስ ቅዱስ፦
በአንደኛ ዬሐንስ መልዕክት 2፣ 18-20 መንፈስ ቅዱስ ቅባት ተብሎ ተጠርቷል። ይህ በአዲስ ኪዳን ከምናገኛቸው ምሳሌያዊ መግለጫዎች አንዱ ነው። ለምሳሌ በዬሐ 20፣ 22 በእስትንፋስ፣ በዬሐ 3፣ 8 በነፋስ፣ በማቴ 3፣ 16 በርግብ ፣ በሐዋ 2፣ 3 በእሳት ፣በዬሐ 7፣ 38 በውኃ ተመስሏል።
መንፈስ ቅዱስ በተለያዩ ነገሮች ምሳሌያዊ በሆነ አገላለጽ መመሰሉ ፣ መለኮታዊ ተግባሩን በሚገባ መንገድ ለመግለጽ እንጂ፣ መለኮታዊ ማንነቱን የሚወክል አይደለም። በዚሁ መሠረት መንፈስ ቅዱስ በቅባት የተመሠለው ለእግዚአብሔር የሚለየን ( የሚቀድሰን) እርሱ መሆኑን ለማመልከት ብቻ ነው።
1.2.3 ክርስቶስና አማኞች፦
እንደ አዲስ ኪዳን ትምህርት ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀባው ካህንም ፣ንጉስም ፣ ነቢይም ተደርጎ ነው።ቃሉ ባህሪውን ሳይሆን ቢሮውን አመልካች ነው። ኢየሱስ ከዘላለም የነበረ እንደመሆኑ ከዘላለም የተቀባ ነው። በሰው ልጅ ታሪክም ውስጥ በዬርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተቀባ( ማቴ 3፣ 16-17፤ ሐዋ 10፣ 38)። የኢየሱስ ክርስቶስ ዓይነት መቀባት የተቀባ በአዲስ ኪዳን ምንም የለም። ወደ ፊትም አይኖርም።
ወደ አማኞች ስንመጣ ግን ፣ አማኞች በሙሉ በመጠን ሳይለያይ የተቀቡ መሆናቸው በ2ቆሮ 1፣ 21 ፤ በ1 ዬሐ 2፣ 20 እና በ1ዬሐ 2፣ 27 ተመልክቷል።ይህም በክርስቶስ በመሆናቸው ብቻ ያገኙት ነው፤ሌላ ምክንያት የለውም። አማኞች በክርስቶስ ባመኑ ጊዜ የቅባቱ ተካፋይ ሆነዋል በሮሜ 8፣ 9 ላይ “ የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም ‘’ ይላል። ሌላው ቀርቶ እኛ አማኞች የተቀባንበት መንፈስ ቅዱስ እንኳን ምስክርነቱ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው( ሐዋ 15 ፡ 16፡ 13- 15)። ቅባት በአዲስ ኪዳን በክርስቶስ በማመን ከተቀበል ነው ከመንፈስ ቅዱስ ውጭ በምንም መልኩ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም። ይህ ለደቀ መዛሙርቱ የእምነታቸውና የአገልግሎታቸው መሠረት ነበር( ማር 8፣ 29፤ ማቴ 16፣ 13- 20፤ ሐዋ 5፣ 42 ፤ ሐዋ 2፣ 34-36)።
1.3 ቅባትና መንፈሳዊ ( የጸጋ )ስጦታዎች፦
በአዲስ ኪዳን ቅባትና መንፈሳዊ (የጸጋ )ሥጦታዎች ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በአዲስ ኪዳኑ ነገረ- መለኮት “ቅባት’’ አንድ ሲሆን መንፈሳዊ ስጦታዎች ግን የተለያዩ ናቸው « የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው»(1ቆሮ 12፣ 4 )። ስለሆነም እንደ አዲስ ኪዳን ትምህርት አንዱ አማኝ ከሌላው አማኝ የተለየ ጸጋ እንጂ ፣ የተለየና በደረጃው ከፍ ያለ ቅባት የለውም። የተቀበልነውም ሆነ የጠጣነው መንፈስ አንዱን ነው።«አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና።ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል(1ቆሮ 12፣ 13) »።
1.4 ስለ ቅባት የዘመናችን አስተምህሮ፦
በዘመናችን የተለያየ የቅባት ዓይነትና ደረጃ እንዳለ ይነገራል። ይኽውም “አዲስ ቅባት” “ልዩ ቅባት” ወዘተ....የሚል ነው። የአዲስ ኪዳን መጽሓፍት ግን ፈጽሞ የተለያየ ዓይነት የቅባት ደረጃዎች እንዳሉ አይናገርም። እንዲህ ዓይነት እምነትና ልምምድ ካለ ትምህርቱ በቀጥታ ከቃለ- እምነት አስተማሪዎች አስተምህሮ ጋር ይያያዛል። የቅባት ደረጃ የሚል አመለካከት በአማኞች መካከል ካለ ልዩነት በማምጣት የበላይና የበታች፣ ገዥና ተገዥ እንዲሁም አስገባሪና ገባሪን እየፈጠረ የሚሄድ ይመስላል። በአዲስ ኪዳን ላይ የተቀመጠልን ግልጽ እውነታ ግን ከዚህ ፈጽሞ በእጅጉ የራቀ ነው።«የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ( ቅባት) ግን አንድ ነው፤አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው (1ቆሮ 12፣ 4-6) የሚል ነው።
በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ስለ ቅባት የሚናገሩትን ጥቅሶች ስንመረምር፣. በየትኛውም ስፍራ ቅባት እጅ በመጫን ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ሲተላለፍ፣ ወይም ደግሞ አንድ ሰው ቅባት እንዴት እንደሚያገኝ ወይም ቅባቱን እንዴት እንደሚያጣ የተሰጠ መመሪያ አናነብም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያቱ እንዴት እንደምንቀባ ያስተማሩት ትምህርት የለም። አንዳንድ አስተማሪዎች ግን ስለ መንፈስ ቅዱስ ሙላትና በከበረው እጅ መጫን ሥርዐት የጸጋ ስጦታዎች ስለ ማነሳሳት የሚናገሩትን የመጽሓፍ ቅዱስ ጥቅሶች በመውሰድ እጅ በመጫን ቅባት ከአንድ ሰው ወደ ሌላኛው ሰው እንደሚተላለፍ ለማስረዳት ይሞክራሉ። ዳሩ ግን የእጅ መጫን አገልግሎት የሚያመልክተን ሰጭው እግዚአብሔር እንደሆነ እንጂ ሰውዬው ያለ መሆኑን ነው። ሲሞን ሰጭው ሰው እንደሆነ በማሰቡ በጴጥሮስ ተገስጿል( ሐዋ 8፣ 18-19)።
ዳሩ ግን በቅባት ላይ ላሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች መስፋፋት ዋና ምክንያቱ የቃለ እምነት አስተማሪዎች እምነትና የእምነት ፍልስፍና ነው። ትምህርታቸው በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል፦
4.1.1. ቅባት የእግዚአብሔር ኃይል ነው፦
የቃለ- እምነት አስተማሪዎች «ቅባት» የእግዚአብሔር «ኃይል» ነው በማለት ያስተምራሉ። በአስተምህሮአቸውም የደረሱበት ድምዳሜ መንፈስ ቅዱስ ይቀባል፤ መንፈስ ቅዱስ ለአማኞች ኃይል ይሰጣል፣ስለዚህ «ቅባት» የእግዚአብሔር ኃይል ነው የሚል ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ
አማኞች በእግዚአብሔር የኃይል ሙላት ውስጥ ልንሆንም ላንሆንም እንችላለን። ዘወትር በመንፈስ እንድንሞላም የታዘዝነው ለዚህ ነው( ኤፌ 5፣ 18)። ነገር ግን በክርስቶስ በማመናችን ምክንያት ዘወትር ከእኛ ጋር ስለሚኖር መንፈስ ቅዱስን( ቅባቱን) ልናጣ ወይም ከእኛ ሊለይ አንችልም ( ዬሐ 14 ፣ 14-15)። ስሙ በሕይወት መጽሓፍ የተጻፈ ክርስቲያን ሁሉ የተቀባ (በመንፈስ ቅዱስ የታተመ) ነው። አማኞች ሁሉ የንጉስ ካህናት ሆነን ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየን ነን። ነገር ግን ከንጉስ ካህንነታችን አልፈን በመሄድ የሊቀ ካህኑን የኢየሱስ ክርስቶስን ስፍራ ልንይዝ አንችልም።
በቃለ- እምነት አስተማሪዎች ስለ ቅባት ያለው የአስተምህሮ ችግር፣ በከፈል መጽሓፍ ቅዱሳዊ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስን የኃይል ሙላት «ቅባት» በሚለው ቃል በመተካት የተፈጠረ የቃላት አጠቃቀምና ውዥንብር ነው። የቃለ እምነት መምህራን ስለ ቅባት ያለ አስተምህሮ ችግር ጎጅነቱ ግን ከዚያ ያለፈና በአስተምህሮው ፍልስፍና የተበረዘ መሆኑ ነው። ስለ ቅባት ባላቸው አስተምህሮ ሲናግሩ « ቅባት በምንናገረው ቃል ላይ ይወሰናል፤ እኔ በነቢይነት ቅባት እነግራችኋለሁ ብዬ በእምነት እስካልተናገርኩ ድረስ እግዚአብሔር አይንቀሳቀስም፣ ምክንያቱም ራሱ እግዚአብሔር ከራሱ ጋር የምንሠራ ሠራተኛ አድርጎናልና » እስከማለት ደፍረዋል። እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይኸውም እግዚአብሔር የሚቀባን በእኛ ቃላት በነቢያት መንፈስ እንዲህ እላችኋለሁ ብለን በመናገራችን ሳይሆን፣ እንዲያው በጸጋው ብቻ በኢየሱስ ክርስቶስ ከፈጸመልን የማዳን ሥራ የተነሳ ነው። ለእግዚአብሔር ቅዱስ ካህናት አድርጎ ለአገልግሎት እንድንለይ ያደረገን የክርስቶስ የማዳኑ ሥራ ነው( ኤፌ 2፣ 8- 10)።
4.1.2 ቅባት ደረጃዎች አሉት?፦
በዘመናችን ቅባትን ደረጃ በደረጃ እየተቀበልን እንመጣለን የሚለው ትምህርት እየገነነ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ እንደ ምሳሌ የሚቀርበው የዳዊት የመቀባት ደረጃዎች ናቸው። ይሁን እንጂ በ1ሳሙ 16፣ 12-13 በእግዚአብሔር ትዕዛዝ በነቢዩ ሳሙኤል በተቀባ ወቅት የእግዚአብሔር መንፈስ እንደወረደበት ከምናይ በስተቀር በ2ሳሙ 2፣ 4-7 ሆነ በ2ሳሙ 5፣ 3 ሲደጋገም አንመለከትም።
የቃለ - እምነት አስተማሪዎች ግን የለምጽ ቅባት፣ የክህነት ቅባትና የንጉሥነት ቅባት በማለት የተለያየ የቅባት ደረጃዎች እንዳለ ያስተምራሉ። እነዚህን ሦስት የቅባት ደረጃዎችንም ሲገልጿቸው « የለምጽ ቅባት የመጀመሪያው ደረጃ ቅባት ሲሆን፣ እያንዳንዱ አማኝ ዳግም በተወለደ ጊዜ የተቀበለው ከድነት ጋር የተያያዘ ቅባት ሲሆን፣ ሁለተኛውና ከመጀመሪያው ደግሞ ላቅ ያለው የክህነት ቅባት ነፍሳትን ወደ ጌታ መማረክን የያዘ ፣ነገር ግን በበሽታና በሰይጣን ላይ ድል ለመቀዳጀት የሚያስችል የክህነት አገልግሎት ቅባት ነው ይሉታል » ሌላው ወይም ሦስተኛው ከሁሉም የላቀውና አማኞች ሁሉ ሊፈልጉት የሚገባቸው የንጉሥነት ቅባት ነው። እንደ መምህራኑ አገላለጽ፤ ይህ የቅባት ደረጃ አንድ የእምነት ቃል ብቻ በመናገር ጠላት ዲያብሎስን ለማባረር ወደሚያስችል ወደ ከፍተኛ ሥልጣንና የኃይል ሙላት ውስጥ የሚከታቸው ነው።
እነዚህ አስተማሪዎች ሦስቱን የቅባት ዓይነቶች ከብሉይ መጽሓፍት በሽተኞች፣ ካህናትና ነገሥታት ከሚቀቡት ቅባት እንደወሰዷቸው ለማስረዳት ይሞክራሉ። ነቢያት ስለሚቀቡበት ቅባት ግን ምንም አይሉም። ምንም ይበሉ ምንም መጽሓፍ ቅዱስ ግን ቅባት ደረጃዎች እንዳሉት አያስተምርም። በአዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ ርግብ ፣ ውኃ፣ በእሳትና በነፋስ እንደተመሰለ በቅባትም ተመስሏል። ቅባት ደረጃ አለው ማለት መንፈስ ቅዱስ አንድ ሆኖ ሳለ ደረጃ እንዳለው ይቆጠራል። ይህ ደግሞ ትልቅ ነገረ- መለኮታዊ ስህተት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ስህተት እንዴት ልፈጠር ይችላል?
አንድ በጌታም ሆነ በእድሜ የሚበልጠኝ የቀደሞ ዘመን ወዳጅ ፣ ዓለም አቀፍ ወንጌላውያን ሥነ መለኮት ኮሌጅ ሄዶ በመጣበት ጊዜ «መጽሓፍ ቅዱስን ሕጉን ጠብቀን ልንተረጉመው ይገባናል ያ ካልሆነ ግን እንደ ባለ ቅኔዎች ክራር የየራሳችንን ቅኝት እንሰጠዋለን የሚለው አባባሉ » አሁን አሁን በብዙዎች ዘንድ እውነት ሆኖ ስላገኘሁት በጣም ይገርመኛል። አባባሉም በጣም እውነታነት አለው ። ከላይ የተመለከትናቸው ችግሮች የራስን ሓሳብ በመጽሓፍ ቅዱስ ላይ ከመጫን፣ በመገለጥ እውቀት ስም ክፍሉን ለማመሳጠር( አላጎሬ ለማድረግ) ከመፈለግና የአፈታትን ሕግ ካለማወቅ የመጣ ችግር ካልሆነ በስተቀር ምን ሊሆን ይችላል? የስህተት ትምህርቶችና ልምምዶች የሚነሱት ከተሳሳተ አተረጓጎም ነው።
የተሳሳተ ትርጉም ካለ የተሳሳተ የሕይወት ተዛምዶ አለ። የሚገርመው ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከምዕመኑም በላይ አገልጋዬችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቃሉን ሳይመረምሩ እንዲያ ማለት ሳይሆን አይቀርም ብለው በቀጥታ ተቀብለው ሥራ ላይ ማዋላቸው ነው። እንዲህ ይሆንን ? ብሎ ወደ ቃሉ በመመለስ የሚመረምር ትውልድ የለም። በዚህ ዘመን የዋሓን ምዕመን፣ የስህተት አተማሪዎችና ተካታዬቻቸው መናጆ ሆነዋል። እግዚአብሔር በገዛ ደሙ በዋጃት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከራሱም ሆነ ለመንጋው የሚተነቀቅ መሪ እየጠፋ የመጣበት ዘመን ነው። « ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ » የሚለው ማሳሰቢያ ፈጽሞ ስለተዘነጋ በባላደራነት ከጌታ የተቀበሉትን ምዕመናቸውን ለተኩላዎች አጋልጠው የሚሰጡ አልታጡም( ሐዋ 20፣ 28)።
ብዙ እረኞች ባሉበት መንጋውን ጠባቂ ጠፍቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም ። ብዙ ጊዜ ለፕሮግራሙ መሸፈን እንጂ ከመድረኩ ለሚተላለፈው ትምህርት ማንም ግድ አይሰኝም። የዘመናችን ሰባኪዎች በሓሳባቸው ፈጽሞ የማይገናኙ ጥቅሶችን እንደልባቸው እየመዥረጡ በኩምክና ቃላት አስፈንድቀውና ኮምከው ሲወርዱ ነው እንደሰበኩ የሚያስቡት። ሕዝቡም ከት ብሎ የሳቀ እለት ነው የተማረ የሚሚስለው። በሁሉ አቅጣጫ በቤተ ክርስቲያን በወንጌሉ ላይ የቆመ አስተማሪና ተማሪነት እየጠፋ ነው። ብዙዎቹም የጠለቀ እውቀት ስለሌላቸው የስህተት ትምህርትና አስተማሪ እንዳለ የሚመስላቸው «የመጠበቂያ ግንብ እምነት» እና «የኢየሱስ ብቻ» ትምህርት ተከታዮችን ሲመለከቱ ብቻ ነው።
ይህንን ሓሳብ ከማጠቃለሌ በፊት አንድ ነገር ልብ እንበል። ይኸውም እንደ አዲስ ኪዳን ትምህርት በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን የተጠሩ የንጉስ ካህናት መሆናቸውን ነው ( 1ጴጥ 2፣ 10-13)። እንደ ክርስቶስ ስጦታም መጠን ሁሉም የጸጋን ስጦታዎች ተቀብለዋል( 1ጴጥ 4፣ 10፣ ኤፌ 4፣ 7፤ 1ቆሮ 12፣ 7- 11፤ ሮሜ 12፣ 3-8)። እነዚህ ስጦታዎች በመንፈስ ቅዱስ ሙላት ውስጥ ሆነን በመንፈስ በመመላለስ፣ ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ ለእግዚአብሔር ክብር እንዲውሉ ማድረግ ይኖርብናል። ምንም እንኳ ከሰው ተፈጥሮ የተነሳ ለአገልጋዮች የተለያየ ደረጃ መስጠት የተለመደ ነገር ቢሆንም ሁላችን ግን እንደ እግዚአብሔር ልጆች በእኩል ደረጃ ያለን ነን።
5. ቅባት ይተላለፋል?
ቅባት ይተላለፋል ማለት መንፈስ ቅዱስ፣ መንፈሳዊ ሥጦታዎች ፣ ሥልጣንና ኃይል ይተላለፋል እንደ ማለት ነው።
5.1 መንፈስ ቅዱስ አይተላለፍም፦
ከሐዋርያት ሥራ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት ሰዎች ልምምድ ስንመለከት መንፈስ ቅዱስን ስለ ተቀበሉበት ሁኔታ ሉቃስ ሲተርክልን ወረደባቸው፣ ፈሰሰና ተሞሉ የሚሉን ቃላት እናገኛለን እንጂ ተላለፈባቸው የሚል አናነብም። ሐናንያ ሳውልን« መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ እንጂ እሞላብህ ዘንድ ላከኝ አላለም » ( ሐዋ 9፣ 17)። ከበዓለ ሐምሳ በፊትም ሆነ በኋላ መንፈሱን የሚሰጥ ራሱ እግዚአብሔር ነው። ደግሞም መንፈስ ቅዱስ አካል ያለው ማንነት ነውና አይሰፈርም፤ አይቆነጠርም፤ አይባዛም።
5.2 መንፈሳዊ ስጦያዎች አይተላለፉም፦
«... አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል... »( 1ቆሮ 12፣ 11) ። አንዱ አማኝ በሌላው ሕይወት ከሚያየው ወይም እግዚአብሔር ካመለከተው ሌላውን ምን ዓይነት ጸጋ እንደሌለው ሊነገረው በአገልግሎትና በአጠቃቀሙ በእግዚአብሔር ቃል ሊረዳው ይችል እንደሆነ እንጂ ጸጋን ማከል የመንፈስ ቅዱስ ብቸኛ ሥራ ነው።
5.3 ሥልጣን አይተላለፍም፦
በብሉይ ኪዳን መሪነት ለማገልገል እንጂ በሌላው ላይ ለመሠልጠን አይደለም። ወንበርም የትድግና እንጂ የመበቀያ አይደለም ። በክርስትናውም ዓለምም እንደ ሂንዱ ጎሳዎች አማኞችን በራሳቸው ፍቅር እየሞሉ « በመንፈሳዊ ሥልጣን» ስም ታማኝ ሎሌዎችን የማፍራቱ አዝማሚያ እየታየ ነው። የሥልጣን አስተላለፍ አድርጎ ራሱን በማቅረብም ሰዎችን ከበታች የማቆየት ዓይነት አሠራር እየተንፀባረቀ ነው። በአዲስ ኪዳን በእግዚአብሔና በምዕመናን እየተመረጡ ሰዎች መሪነት ያመጡ እንደ ነበር በግልጽ የሚታይ ነው።
5.4 ኃይል አይተላለፍም፦
የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከእርሱ ተነጥሎ የሚሠራ አይደለም። በሐዋ 1፣ 8 ላይ « .....ኃይልን ትቀበላላችሁ ብሎ» 2፣ 4 ላይ ደግሞ« መንፈስ ቅዱስን ሞላባቸው » ይላል። ኃይል ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ እየተሰለፈ አድሮ እንደሚሠራ ከታመነ ተቀባይ ኃይልን ለወደደው ጉዳይ የማዋል ነፃነት እንዳለው ይመስላል። የመንፈስ ቅዱስን ባለቤትነት የሚያስቀር ያለ ሥራም መገኜትና ቀጥተኛ ምሪት የሚሆን የጸጋ ሥጦታና የኃይል ልምምድ በጥያቄ ውስጥ ሊቀመጥ ይገባል።
6. ሁለት እጥፍ ቅባት፦
ቀደም ብዬ ለመጠቆም እንደሞከርኩት የቃለ - እምነት አስተምህሮ አስተማሪዎች አንድ አማኝ ከለምጽ ቅባት ወደ ክህነት ቅባት ፣ ከዚያም ወደ ንጉሥነት ቅባት የሚሸጋገር ብቻ ሳይሆን ፤ ሁለት እጥፍ ቅባትና ሁለት እጥፍ ኃይል ሊቀበል እንደ ሚችል ያስተምራሉ። እነዚህ መምህራን እንዲህ የሚሉት እንዲህ ዓይነቱን አስተምህሮ በማመሳጠር / አላጎሪ / በማድረግ ከቀደመው ኪዳን ሥርዐት ተወስዶ በአዲሱ ኪዳን ተዛምዶአዊ ፍች ለመስጠት ሲሞከር በተፈጠረ የቅዱሳት መጽሓፍት አፈታት ችግር እንደሆነ ቀደም ብዬ ጠቁሜአለሁ ።
መምህራኑ ስለ ሁለት እጥፍ ቅባት የሚናገሩት ስለ ኤልያስና ኤልሳዕን ከተጻፈው ክፍል በመነሳት ነው። ኤልያስ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ኤልሳዕን የቀባው የነቢይነት አገልግሎት እንዲቀጥል ለማድረግ ነው( 1ነገ 19፣ 16)። እዚህ ላይ ታዲያ አንድ ጥያቄ እናነሳለን ። ይኸውም ኤልሳዕ የተቀባው ሁለት እጥፍ ቅባት ነበረ ወይ ? የሚለውን ይሆናል። በፍጹም። የቅባት ደረጃ የለም። እውነታው ወይ ተቀብቷል ወይም አልተቀባም ነው። እንዲህ ከሆነ ታዲያ ይህ የሁለት እጥፍ ቅባት ሓሳብ ከወዴት መጣ? ቀደም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የቃለ እምነት አስተማሪዎች ቅባትና የመንፈስ ቅዱስን ኃይል አንድ አይነት አድርገው ስለሚወስዱት ነው። ክፍሉ በትክክል ሲጠናም ኤልሳዕ ኤልያስን የጠየቀው ሁለት እጥፍ መንፈስ እንጂ ሁለት እጥፍ ቅባት አይደለም። በክፍሉ ሁለት እጥፍ ተብሎ የተገለጸው ቃል« እንደገና ማድረግ ተብሎ ሊተረጎም የሚችል» ሲሆን፣ «መንፈስ» የሚለው ቃል ደግሞ ትንቢታዊ ቃል ለመስጠት የሚያችል ማለት ነው። ስለዚህ የኤልሳዕ ጥያቄና የተቀበለውም የኤልያስን አገልግሎት ተክቶ መስራት የሚያስችለውን የትንቢትና የታዕምራት አገልግሎት ነው።
እንደ መምህራኑ ትምህርት ቅባት በአማኞች ሕይወት የሚለቀቀው በሦስት መንገድ ሲሆን፣ ይኸውም 1. በትክክለኛው ስፍራ በመገኘት 2. ቅባቱ የሚፈሰው ከሰብዓዊ መሪዎች ሲሆን፣ ለትክክለኛው ቅባት ከትክክለኛው መሪ ሥር በመሆን 3. ቅባቱ እንዲመጣ ሁል ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ በመረስረስ እንደ ሆነ ይናገራሉ። ለመጀመሪያው ነጥብ ምንም መጽሓፍ ቅዱሳዊ መነሻ የላቸውም። ይሁን እንጂ አስተሳሰቡ እግዚአብሔርን በቦታ፣ እንደገናም መለኮታዊ ኃይሉን የሚገድብ አስተሳሰብ ነው። ሦስተኛውን ሓሳብ ደግሞ የሚወስዱት ከ2ነገ 6፣ ላይ ካለው ክፍል ሲሆን፣ ክፍሉ ኤልሳዕ አንድ እንጨት ቆርጦ ውኃ ውስጥ በመጣል መጥረቢያው በውኃው ላይ የተነሳፈፈበትን ሁኔታ የሚተርክ ነው። ይህንን ክፍል ሲገልጹ ደግሞ እኛ እንጨቱ የመጥረቢያው ጫፍ ደግሞ ቅባቱ ነው በማለት ያስተምራሉ። ክፍሉ ማንም በቀላሉ ሊረዳው የሚችል ክፍል ነው። በዚህ ክፍል የምንመለከተው ነብይ ድሃ ነበር። መጥረቢያው ሲሰጥምበት የጮኸውም መክፈል ስለማይችል ነበር። ድሃ የሆኑት ቅባት የሌላቸው አማኞች ናቸው እስከ ማለት ለደረሱት ለቃለ እምነት- አስተማሪዎች ይህ ሊታያቸው አይችልም። የመጥረቢያው ራስ ቅባትን የሚል ነው ብለን እንድንተረጉም ምንም የሚያስችለን ነገር በክፍሉ የለም።
7. የተቀባ ልሣን የሚባል አለ ወይ ?
ቀደም ብለን ለማየት እንደሞከርነው በቅዱሳት መጽሓፍት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በርግብ፣ በቅባት፣ በውኃና በእሳት ስያሜ ተጠቅሷል ( ማቴ 3፣ 16፤ ዬሐ 3፣ 8፤ 7፣ 38፤ ሐዋ 2፣ 2፣ 3፣ 1ዬሐ2)። መንፈስ ቅዱስ ቅባት በሚል ስያሜ ሲጠራ፣ ቅባት ከመንፈስ ቅዱስ ተነጥሎ የሚታይ ሌላ ታዕምር ሆኖ አይደለም። ይሁን እንጂ በዚህ ዘመን ቅባትን ከመንፈስ ቅዱስ ነጥሎ የመመልከቱ ጽንፍና አመለካከት አንዳንዶችን ስለሚጸልዩት ልሳን የተለየ ግምት ውስጥ እንዲገቡ እያደረጋቸው መጥጧል። መንፈሳዊ ስጦታዎች በሕይወታችን ቢገለጡ ፣ጌታም በሕይወታችን በጸጋው አንዳንድ ምልክቶችን ቢያደርግ የጸጋውን አሠራር ለማሳየት እንጂ አንዳንዶች በወፍራምና በተቀባ ልሣን ሌሎች ደግሞ ባልተቀባና በቀጭን( እንደ ውኃ ሽርር ባለ) ልሳን ይናገራሉ በማለት በክፍል ወይም በደረጃ እንድንመድብ አይደለም።
ውድ አንባቢያን ! ከዚህ በታች የማቀርብላችሁ በአንድ ወቅት ገጥሞኝ የነበረውን ጥያቄ ነው። ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን በተከታታይ የሚሄድ አንድ በጌታ የቆየና አስተዋይ የሆነ ክርስቲያን ወንድም፣ አንድ ጊዜ እንዲህ የሚል ጥያቄን ጠየቀኝ። አንተ የረዥም ጊዜ አገልጋይ ደግሞም ጥሩ የቃሉ አስተማሪ እንደሆንክ አያለሁ ፤አልፎ አልፎም መልዕክቶችንህ እሰማለሁ ፤ ትምህርት አዘል ጽሁፎችህ ግን ምንም አይቀረኝ ፤ ሁሉንም እያሳደድኩ እቃርማለሁ። ስለዚህ በጉባኤ ላይ የምመለከታቸውንና ግራ የምጋባባቸውን ጥያቄዎች ልትመልስልኝ ትችላለህ? ብሎ ጠየቀኝ።
ጥያቄዎችም እንዲህ የሚሉ ነበሩ። « በምሄድበት ጉባኤ ( ቤተ ክርስቲያን) የእለቱ ሰባኪ በስብከቱ መሓል እንዲህ አለ « የእኔ ልሳን ወፍራምና የተቀባ ልሳን ስለ ሆነ አጋንቶች ይፈሩታል፣ መናገርም ስጀምር ሽብርም ይለቅባቸዋል» በማለት ስለሚጸልየው የልሳን ዓይነት ድምጹን ወፈር አድርጎ «ኮራ ሞዳ፣ ኮቶ ሞኒ ሽንኪሊሊ ቦዬ» በማለት ወፍራምና የተቀባ አጋንንት አስደንጋጭ የሚለውን የልሳን ዓይነት ናሙናውን( ሳምፕሉን) በረዥሙ በስብከት መሐል በመልቀቅ አሰማን። ወዲያውም ከጉባሌው አንዳንዶች በስሜት አሜንታቸውን በረዥሙ በማሰማት አጸፋዊ ምላሻቸውን ሰጡ። ጉባኤውም ትርጉሙን ባልተረዳው ልሳን ተባረክሁ ያለ ይመስላል። እልልታውንና ጭብጨባውንም አቀለጠው ። በመሓል ሰባኪው እስኪ እንደገና የገባው አንድ ሰው እንደ ገና “አሜን” ይበል ሲል፤ ጉባኤውም እንደ አንድ ሰው አሜን በማለት እንደገባው ምላሽ ሰጠ።
በመሠረቱ በዚያን ዕለት የሰማሁት ወፍራም ልሳን ሳይሆን ለዚያን ሰዓት ደራማ የተቀየረ ወፍራም ድምጽ ነው። የእኔ ጥያቄ ግን ልሳን ከመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎች አንዱ ነው። ይህንንም አምናለሁ። መንፈስ ቅዱስም ሲሰጠን ብቻ እንናገራለን ( ሐዋ 2፣ 1-4) የእኔ ጥያቄ ግን « የተቀባ ልሳን» ስለሚባል ነገር ከመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ አንብበሃል ወይ? መጽሓፍ ቅዱስ ስለ እዚህ ሁኔታ ምን ይላል? አጋንንትም ከሰዎች የሚወጡት ክርስቶስ ሁሉ ከእግሩ በታች ስለተገዛለት በስሙ ሥልጣን እንጂ፣ አገልጋዩ ማይክ ይዞ እንደ ነጎድጓድ እያስገመገመ በሚጸልየው ልሳን ነወይ? አጋንንቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሰው እንዲወጡ ይታዘዛሉ ፤ለመሆኑ በልሣን መገሰጽ የሚባል ነገር አለ?
ደግሞስ የሚተረጎምና ሓሳቡን በቋንቋችንና በአእምሮ ተረድተነው አሜን የማንል ከሆነ፣ እንደ አዝማች በቃሉ ስብከት መሐል« ኮራ ሞዳ፣ ኮቶ ሞኒ ሽንኪሊሊ ቦዬ » እያሉ መናገሩ ለምን አስፈለገ? ጉባኤውስ ተተርጉሞለት ሓሳቡን ሳይረዳ ምኑ ገብቶት ነው ድምጹን ከፍ አድርጎ አሜንታውን የሚያቀልጠው? እንዲህ ከሆነ ዳግማዊ ቆሮንቶሳውያን መሆናችን አይደለምን?። እነርሱ በሐዋርያት ሥልጣን በተጻፈላቸው መልዕክት ከደብዳቤው ሓሳቡን ተረድተው የተሰተካከሉና የታረሙ ይመስለኛል። እኛ መጽሓፉ በእጃችን አያለ የምንታረመው እስከ መቼ ነው? የእኔ ሓሳብ የሚተረጎም የልሳን ዓይነት እንደገናም ሰው በግሉ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት የሚነጋገርበትና ራሱን የሚያንጽበት ልሳን የለም የሚል አይደለም( 1ቆሮ 14፣ 2-3)። እኔ ጥያቄ የሚሆንብኝ የማይተረጎምን ልሳን በስብከት መሐል እንደ ናሙና እየተናገሩ ጉባኤን በስሜት ማሳበድ ከቃሉ አኳያ ልክ ነውይ? ሰባኪዎቻችንስ እስከ መቼ ነው? በሰው ስሜት ላይ ከሚርከፈከፍ ስብከታቸው ወጥተው የሰውን አእምሮ የሚለውጥ የወንጌል ቃል የሚያቀርቡልን? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከመንፈሳዊ ጨቅላነት የተነሳ ሥርዐተ አልበኝነት ይታይባቸው ለነበሩ የቆሮንቶስ አማኞችን መንፈሳዊ ሥጦታዎችን በአግባብ መጠቀም እንዳለባቸው ሲናገር « እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ። አብደዋል አይሉምን? ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረ ይገለጣል እንዲሁም። እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል» ( 1ቆሮ 14፣ 23- 25)። እኔ የሚገባኝ የልሳንን ሥጦታ ያለ አግባብ መጠቀም የመንፈሳዊ ጭቅላነት ምልክት እንደሆነ ነው። በዚሁ ክፍል የዚህን ስጦታ አጠቃቀም በተመለከተ« በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ በአእምሮ የበሰላችሁ ሁኑ በማለት ሐዋርያው ተዕዛዝ ሰጥጧል( 1ቆሮ 14፣ 22- 21) ።» ያለ አግባብ ስንጠቀም ብንገኝ ሥርዐተ አልበኛ መሆናችን አይደለምን?
አገልጋዬታችን ግን የመንፈሳዊነት ምልክት አድርገውት እየጸለዩ ሳይሆን እየሰበኩ የተቀባ በሚሉት ልሳን በረዥሙ ይናገሩና አሜን ነው ይሉናል። እኔ ምኑ ገብቶኝ አሜን ልበል? ወንድሜ እስኪ የገባህ ነገር ካለ ንገረኝ ? አገልጋዩ በልሣኑ እያመሰገነ ሊሆን ይችላል ። ጥሩ ነው ። ጳውሎስ ግን « እግዚአብሔርን በመንፈስ በምታመሰግንበት ጊዜ ለነገሩ እንግዳ የሆነ ሰው አንተ የምትናገረውን ካልተረዳ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ሊል ይችላል? አንተ በሚገባ ታመሰግን ይሆናል ሌላው ሰው ግን አይታነጽበትም፤» በማለት ይመክረናል(1ቆሮ 14፣ 16- 17 ) ። ከተተረጎመ መልካም እንታነጽበታለን፤ ሌላው ካልታነጸበት ግን ለምን ቦታ አይፈለግለትም። ታዲያ እኛ ማንን እንመን? ቅዱስ ቃሉን ወይስ አስተማሪዎቻችንን?
ጳውሎስ የቆሮንቶስን አማኞች ከሁላችሁ ይልቅ በልሳን ስለምናገር እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌሎችን ለማስተማር በዐሥር ሺ ቃላት በልሣን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአዕምሮዬ ብናገር ይሻላል» ይለናል( 1ቆሮ 14፣ 18- 19)። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ባልተተረጎመ ልሣን ዐሥር ሺህ ቃላት ከመናገር ይልቅ፣ ሰዎች ሊረዱት የሚችሉትን ጥቂት ቃላት መናገር እንደሚመርጥ ይናገራል። እርሱ ይህንን ከመረጠ እኛ ይህንን የምንመርጥበት ምክንያት ምንድነው? በማለት በጥያቄው ብርጅብኝ አጣደፈኝ። እኔም ጥያቄውን ሲጭርስ ያልኩት “የአንተ ያለህ” ነው።
መቼስ እኔ ምንም ከማለት ይህንን ያለውና ያደረገው አገልጋይ ጠይቆት መልስ ቢሰጠው እንዴት መልካም ነበር። ይሁን እንጂ እንደመጣ እንዳይመለስ በጥያቄ ታጭቆ ለመጣው ወንድም የሚገባኝን ያህል ለመመለስ መክሪያለሁ። የምረዳውም እንዲህ ነው ። በቀደሙት ዘመናት የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ስንጠማና የጌታን ፊት ስንፈልግ የነበረው « ጌታ ኃይልህን አልብሰን ፣ እሳትህን በመካከላችን አውርድ» ነበር። ደግሞም መጽሓፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ጸሎት ይመስለኛል( ሐዋ 1፣ 8)። ከዚህ ውጭ ቅባትህ ይውረድብኝ፣ ባለ ደረጃ ቅባት ፣ መንፈስ ቅዱስ አንደሰጠን በቅባት የረሰረሰ ወፍራም ልሣን ወዘተ የሚባል ነገር አልነበረም። ባማርኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት «ልሳን» ማለት አንደበት፣ ቋንቋ ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስም ታዕምራዊ በሆነ መንገድ በእኛ የጸሎት ሰዓት የእኛ ባልሆነ «አንደበት» ቋንቋ እንድንጸልይ ሊያደርገን፣ እንዲሁም ከተተረጎመ ብቻ በዚያም ውስጥ ጉባኤውን ሊያንጽ የሚችል መልዕክት ሊያመጣ ይችላል። ሥጦታውን የጸጋ የሚያደርገው ሳንማረው ልሳንን ወይም ቋንቋን መናገር መቻላችን ነው።
ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች አጠቃቀም በስፋት የተዘረዘረልን በ1ቆሮ 12- 14 ባለው ክፍል ነው። ከእነዚህ ምዕራፎች በተለይም ምዕራፍ አሥራ አራት ላይ ስለ ልሳን አጠቃቀም ይናገራል። በዚህ ክፍል ጳውሎስ ካልተተረጎመ ልሣን ይልቅ ትንቢት ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያንጽ( 14፣ 1-4)፣ ትንቢትና የተረጎመ ልሳን ለቤተ ክርስቲያን እኩል አስፈላጊዎች እንደሆኑ( ቁጥር 5)፤ ያልተተረጎመ ልሳን በጉባኤ ውስጥ ምንም ዓይነት ጥቅም እንደሌለው ( ቁጥር 6- 12)፤ በጉባኤ በልሳን የሚጸልዩ ወገኖች ጉባኤው ይታነጽ ዘንድ የሚተረጉም ከሌለ እንዲተረጉሙ መጸለይ እንዳለባቸው(ቁጥር 13)፤ በጉባኤ ኃጢአተኞች የእግዚአብሔርን ሀልዎት አውቀው ይወቀሱ ዘንድ ካልተተረጎመ ልሳን ይልቅ ትንቢት የጎላ ሚና እንዳለው( ከቁጥር 20- 25)እና ቤተ ክርስቲያን ትታነጽ ዘንድ በቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ጊዜ በትንቢትና በልሳን መናገር በሥርዐት መሆን እንዳለበት አስተምሯል። ይህንን እውነታ ስንመለከት ሐዋርያው አንድም ቦታ ስለ ተቀባ ልሳን አልተናገረም። እኛ ራሳችንን ከሌሎች ለማብለጥለጥና ነገራችንን ለማመናፈስ የፈጠርነው ማደናገሪያ ካልሆነ በስተቀር፣ መጽሓፍ ቅዱስ አንድም ቦታ እንዲህ ዓይነት ልሳን እንዳለ አያስተምርም። ይህ ስለ ቅባት ያለ የተለጠጠ ትምህርት ውጤት ነው። የቃለ እምነት አስተምህሮ መዘዙ ብዙ፣ የቅዱሳትም መጽሓፍት ሥልጣን ባላጋራ ነው።
በማጠቃለያችን በወንጌላውያን አማኞች ዙሪያ ቅባትን በተመለከተ ለሚታየው መስመር ለለቀቀ ትምህርት ትልቁ ችግር ቅባት የሚለውን ቃል በትክክል ባለ መረዳትና ቅባት ማለት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው ብሎ በመውሰድ የመጣ ችግር ነው። በቅዱሳት መጽሓፍት ያሉትን የመጽሓፉን ክፍሎች በሚገባ ከተመለከትን ግን ቅባት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው ብለን እንድንወስድ የሚያስችለን ምንም ነገረ የለም። ይህንን ጽሑፍ ለመታነቡ ሁሉ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር እግዚአብሔር አማኞችን ሁሉ ቅድሳን ካህናት ስላደረጋቸው የተቀቡ መሆናቸውን ነው። ማናችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እኩል ወይም የመለኮት ቁራጭ ነን ካላልን በስተቀር ከአማኞች ሁሉ ልቀን እንድንታይና በአማኞችና በእግዚአብሔር አማላጅ ሆነን ለመቆም የሚያስችለን የሊቀ ካህን ቅባት አለን ማለት አንችልም። ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ዳሩ ግን ራሳቸውን ክርስቶስ ነን ያሉ ሐሰተኞች የተለየ ቅባት አለን ብለው ቢያስተምሩ መደነቅ የለብንም። ክርስቶስ ማለት የተቀባ ማለት ነው። እኛም ስለተቀባን ክርስቶስ ነን ለሚለው የተሳሳተ ትምህርት በሩን የሚከፍትልን ይኸው ስለ ቅባት ያለ የተዛባ ትምህርት ነው። ለተለያዩ አገልግሎቶች የተለያዩ የአገልግሎት ስጦታዎች አሉ እንጂ የተለያዩ ቅባቶች አሉ ወደሚል የተሳሳተ ድምዳሜ እንዳንመጣ ቃሉን እንመርምር። ስለ ቅባት ስናስብ እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ያዳነን፣ የመረጠን ፣ ለቅዱሱ አገልግሎት በተሰጠን ልዩ ልዩ ጸጋ ስጦታዎች አማካይነት እንድናገለግለው የሾመን ለዚህ የክህነት አገልግሎት የቀባን መሆኑን አውቀን ፣ በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ደስ ልንሰኝ ይገባናል።
ቸር እንሰንብት !!